ከ65 ዓመታት በፊት በፋሺስት ጣሊያን በዝርፊያ ተወስዶ የነበረውን የአክሱም ሐውልት ወደ ሀገሩ ለመመለስ የጣሊያን መንግሥት ፈቅዶት የነበረውን ገንዘብ፣ አሜሪካ ደግሞ የማጓጓዣ አውሮፕላኗን መከልከላቸውን ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አስታወቁ።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁር፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር በየ15 ቀኑ ከሚታተመው "ባላደራ" ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሜሪካኖች ከአምስት እስከ ስድስት ሰዓት ለሚፈጅ በረራ የጠየቁትን አውሮፕላን "ኢራቅ በሥራ ላይ ነው ያለው" በሚል ሰበብ መከልከላቸውን በአግራሞት አስረድተዋል።
"ጣሊያኖች ሮም የሚገኘውን ሀውልት በፈረሙት ቃል መሰረት በ1947 (እ.ኤ.አ) መመለስ ነበረባቸው። ...ነገር ግን ለመመለስ ፈቃደኞች አልሆኑም። ላለመመለሳቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ሀውልቱ ትልቅ ስለሆነ ትራንስፖርት ቸገረን ነው። ለመመለስ ከፈለጉ በሻንጣ ሊመጡ የሚችሉ የሀገሪቱ ውድ ሃብት፣ የመንግስታት መዋዕለ ዜና እና ሰነድ የትም ሊገኙ የማይችሉ መዛግብት አሉ። እነሱን ይመልሱ ነበር። በአንድ ኮንቴይነር ታሽጋ ልትመጣ የምትችል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገጣጠመችውን "ፀሐይ" የምትባል አውሮፕላን ይመልሱ ነበር።ለሁሉም ሰበብ ይፈልጋሉ። አውሮፕላኗ በጣሊያን አቪዬሽን ሙዚየም ውስጥ ትገኛለች። ለሃውልቱ የሚቀርበው የትራንስፖርት ችግርም ቅንነት የጐደለው ምክንያት ነው።" በማለት የምክንያቱን ረብ የለሽነት አጋልጠዋል። አያይዘውም መመለስ አለባቸው። መቅደላ ላይ ይህች አገር የተዘረፈችው። አቻም መተኪያም የላቸውም። መጠየቅ አለባቸው። ዛሬ የሚሰረቁትንም ነገ የኛ ናቸው ለማለት በማይክሮ ፊል ተቀርጸው መቀመጥ አለባቸው" ብለዋል።